ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክበን እንዲጸድቁ እና ፍሬ እንዲያፈሩ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ሰኔ 11/2015 (ዋልታ) ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ እንዲጸድቁ እና ፍሬ እንዲያፈሩ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መርህ ሃሳብ የዘንድሮውን አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ በይፋ አስጀምረዋል፡፡

በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከ41 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ግባችንን አሳክተናል ብለዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 17 ሚሊዮን ሀገር በቀል ዛፎችን፣ ለምግብነት የሚውሉ እና ለውበት የሚሆኑ ችግኞችን ዝግጁ ማድረጋቸውን ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አዲስ አበባን አረንጓዴ በማልበስ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ውብ ከተማ ለማድረግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክበን እንዲጸድቁ እና ፍሬ እንዲያፈሩ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት መሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎችም ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡