የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች የመጀመርያ ዙር የጋራ መኖርያ ቤት ዕጣ አወጣጥ ስነ ሰርዓት ተካሄደ

ሰኔ 11/2015 (ዋልታ) በጤና ሚኒስቴር፣ ጎጆ ብሪጅ ሃውስና ዳሽን ባንክ ትብብር ሲካሄድ የቆየው የጎጆ ሮስካ የጤና ባለሙያዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

በዚህ የመጀመርያ ዙር ዕጣ አወጣጥ ስነ ሰርዓት 7 ሺሕ 582 የዕጣ ተሳታፊዎች የተካተቱ ሲሆን ሁለት መቶ የሚሆኑት የመጀመርያ ዙር የመኖሪያ ቤት ዕጣ ዕድለኞች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት ሚኒስቴሩ በሁለተኛው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ላይ የሰው ሀይል ልማቱን ማሻሻልና ማበረታታት እንደ አንድ ቁልፍ ስትራቴጂክ በመያዝ የተለያዩ የማትግያ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

በዚህም በከተሞች አካባቢ የመኖርያ ቤት ችግሮች እንደሚስተዋል ገልጸው የጤና ሚኒስቴር የሰራተኞችንና የባለሙያዎችን የመኖርያ ቤት ችግርን ለማቃለል ከጎጆ ብሪጅ ሀውስ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና የዛሬው የጋራ መኖርያ ቤት የመጀመርያ ዙር ዕጣ አወጣጥ ስነ ሰርዓትም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጎጆ ብሪጅ ዋና ስራ አስፈጻሚ አልማው ጋሪ በበኩላቸው የዕጣ ማውጣት ሂደቱ በየሶስት ወሩ እንደሚቀጥል ገልፀው በቀጣይም ከዚህ በላይ እየሰፋ ይሄዳል ብለዋል፡፡

በዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓቱ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የዳሽን ባንክ እና የሌሎች ተቋማት ተወካዮች መገኘታቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡