ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ የጸረ-ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ አስጀመሩ

ኅዳር 16/2015 (ዋልታ) የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የዘንድሮውን የ16 ቀናት የጸረ-ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ በይፋ አስጀምረዋል።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ በወቅቱ እንደተናገሩት በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም አመለካከቱንና ድርጊቱን በጽኑ ሊያወግዘው ይገባል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ችግሩን ለመቅረፍ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ለተግባራዊነቱ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ያደነቁት ፕሬዝዳንቷ፤ ችግሩ በዘላቂነት እንዲስተካከል ጥቃት የሚፈፀምባቸው ሴቶችና ህጻናት ፍትህ እንዲያገኙ መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ በየዓመቱ የሚካሄድ ዘመቻ ነው።

ዘመቻው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 01 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ባሉት 16 ቀናት የሚከናወኑ ሲሆን ውይይቶች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቀናቱ በፆታዊ ጥቃት ምክንያት የሚከሰቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥና ችግሩን በዘላቂነት መከላከል የሚቻልባቸው ተግባራት ላይ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ ተመላክቷል።

በተለይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በአካባቢያቸው ለሚገኙ ሴቶች ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ ማሳሰብንስራን እንደሚያካትትም ተገልጿል፡፡