ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ የሲቪክ ማህበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

                                             አቶ ሄኖክ አሻግሬ

ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ የሲቪክ ማህበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሲቪክ ማህበራትና የህግ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

ዋልታ ያነጋገራቸው የሲቪክ ማህበራትና የህግ ባለሙያዎች 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሲቪክ ማህበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል በሀገሪቱ በተካሄዱ ምርጫዎች ላይ የተስተዋሉ እንከኖችን በማረም ስልጣን በህዝብ ምርጫ ብቻ የሚወሰንበት እንዲሆን የሲቪክ ማህበራት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ካካሄደቻቸው ምርጫዎች በርካታ እክሎችን ማንሳት ቢቻልም ሲቪክ ማህበራት የመታዘብ መብት እንኳን የተነፈጉበት ሁኔታ እንደነበር የህግ ባለሙያው አቶ ሄኖክ አሻግሬ አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት የነበረው አሰራር የሲቪክ የማህበራትን መብቶች የጣሱ ተግባራት ይፈፀሙ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

መራጩ ህዝብ ያለማንም ግፊት ይጠቅመኛል የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ እንድችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን የሲቪክ ማህበራት በንቃት መስራት እንዳለባቸው የህግ ባለሙያው አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማህበራት መካከል አንዱ የሆነው የኖቪፕ  ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌቱ ሙላቱ በበኩላቸው፣ ምርጫው ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ የሲቪክ ማህበራት መራጩን ህዝብ ከማስተማር እና በታዛቢነት  ከመሳተፍ አንፃር ሚናቸው የላቀ ነው ብለዋል፡፡

የኖቪፕ  ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌቱ ሙላቱ

የኢትዮጵያ ሲቪል ሶሳይቲ ጥምረት አባል የሆኑት አቶ ሳህረስላሴ አበበ የሲቪክ ማህበራቱ  ገለልተኛ  በመሆን ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

አቶ ሳህረስላሴ አበበ

(በሄብሮን ዋልታው)