አለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ቀን እየተከበረ ነው

ሚያዝያ 26/2013 (ዋልታ) – አለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ቀን “መረጃ ለህዝበ ጥቅም” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ጊዜ የሚከበረው የፕሬስ ነጻነት ቀን በአዲስ አበባ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ዩኔስኮ አጋርነት በተዘጋጀው መድረክ ቀኑ ሲከበር ሙያውን በማክበር እና ማህበራዊ ግዴታን በመወጣት ሊሆን እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን ከእስር ቤት በመፍታት እና የተለያዩ የውጪ መገናኛ ብዙኃን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ መረጃ ለህዝብ ማድረስ እንዲቻል የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ደረጃ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቧን በኢትዮጵያ የዩኔስኮ ተወካይ ዳይሬክተር ዶክተር ዩኒኮ ዮካዛኒ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነትን ለማሳደግ የመገናኛ ብዙኃን እና ጋዜጠኞች ከወገንተኝነት የራቀ፣ ግልጽ እና ተአማኒ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ ሙያዊ ግዴታቸውን እና ኃላፊነታቸውን መወጣት ይገባልም ተብሏል፡፡
(በሜሮን መስፍን)