የኢትዮጵያ ሳምንት የኤግዚቢሽን እና ፌስቲቫል እንደሚከበር ተገለፀ

ሚያዝያ 26/2013 (ዋልታ) – የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሳምንት የኤግዚቢሽን እና ፌስቲቫል እንደሚከበር ተገለፀ፡፡
ከግንቦት 10 እስከ 16/2013 ዓ.ም የሚከበረው የኢትዮጵያ ሳምንት ኤግዚቢሽን እና ፌስቲቫል በክልሎች መካከል የባህል ሽግግር እንዲኖር ያደርጋል ተብሏል።
አንድ ሳምንት በሚቆየው ኤግዚቢሽንና ፌስቲቫል ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉ ሲሆን፣ በክልሎች ያሉ ሀብት እና እሴቶች ለኢንቨስተሮች ይቀርባሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አቅራቢነት፣ የሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሀላፊነት አዘጋጅተውታል።
የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የኢትዮጵያ ሳምንት የኤግዚቢሽን እና ፌስቲቫል አጠቃላይ የዲዛይን ስራዎች እንደሚቀርቡና አስሩም ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በተገቢው ሁኔታ በተሰጣቸው ስፍራ ባህል እና እሴቶቻቸውን እንደሚያስተዋወቁ ገልጸዋል።
የሴቶች እና ህፃናት ሚኒስትር ወ/ሮ ፊልሰን አብዱላሂ ኤግዚቢሽን እና ፌስቲቫሉ በህዝቦች መካከል አንድነትን ለማጠናከር ብሎም ኢንቨስተሮችን ለመሳብ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ሳምንት ቱሪስቶችን ለመሳብ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ በአገር ደረጃ የተካሄደ ኤግዝቢሽን እና ፌስቲቫል ባለመኖሩ የመጀመሪያው ያደርገዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሳምንት ኤግዚብሽን እና ፌስቲቫል መግቢያ ለአዋቂዎች 100 ብር፣ ለህፃናት ደግሞ 50 ብር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ከመግቢያ ትኬቶች የሚሰበሰበው ገቢ በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ ይውላል ተብሏል።
(በቁምነገር አህመድ)