ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – አሜሪካ ለኢትዮጵያ የለገሰችውን 453 ሺህ 600 ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተረከቡ።
በአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ የተደረገው ድጋፍ “ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን” የተባለው ክትባት ሲሆን፣ ቃል ከገባችው 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶዝ 453 ሺህ 600 ዶዙ አዲስ አበባ ገብቷል።
ድጋፉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ቦሌ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ በመገኘት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ተረክበዋል።
አሜሪካ በሚቀጥሉት ሳምንታት 25 ሚሊየን ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ለ49 የአፍሪካ አገራት ድጋፍ እንደምታደርግ ታውቋል።
በመጀመሪያው ዙር 1 ሚሊየን ዶዝ ለቡርኪናፋሶ፣ ለጅቡቲ እና ኢትዮጵያ ተደራሽ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመከላከል እስከ አሁን ከ2 ሚሊየን በላይ ዜጎች “የአስተራዘኒክ” እና “ሲኖፋርም” የተባሉ ክትባቶችን መስጠቷ ይታወቃል፡፡