አሜሪካ 60 ሚሊየን የሚጠጋ የኮቪድ-19 ክትባት ለተለያዩ አገራት ልትሰጥ ነው

የኮቪድ-19 ክትባት

 

ሚያዝያ 19/2013 (ዋልታ) – አሜሪካ ወደ 60 ሚሊየን የሚጠጋ የአስትራዜኒካ ክትባት ለሌሎች አገራት ልትሰጥ እንደሆነ አስታወቀች።

ክትባቶቹ አስተማማኝነታቸው ተረጋግጦ በቀጣይ ወራት ወደተለያዩ አገራት እንደሚላኩ ተገልጿል።

የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ገና ፍቃድ ያልሰጣቸው በርካታ ክትባቶች አሜሪካ ውስጥ ተከማችተው ሲሆን፣ የተለያዩ አገራት በቂ ክትባት ማግኘት ባይችሉም የአሜሪካ መንግሥት ግን ከሚያስፈልገው በላይ ክትባት እያከማቸ ነው በሚል ሲተች ቆይቷል።

ባለፈው ወር ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አራት ሚሊየን የአስትራዜኒካ ክትባት ለሜክሲኮ እና ለካናዳ ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር።

በሕንድ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ተከትሎ፤ አሜሪካ ያከማቸችውን ክትባት እንድትለግስ ጫና እየተደረገባት እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

ከጠቅላይ ሚንኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር የስልክ ውይይት ያደረጉት ፕሬዝዳንት ባይደን፤ ኦክስጅን፣ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ መሣሪያ፣ ክትባትና ሌሎችም ምርቶችን ለመስጠት ቃል መግባታቸው ተገልጿል።

የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር በቀጣይ ሳምንታት የክትባቶቹን ደኅንነት ፈትሾ ፍቃድ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዋይት ሐውስ መግለጫ ይጠቁማል።

ከዚያም ወደ 10 ሚሊየን የሚጠጋ የአስትራዜኒካ ክትባት ወደተለያዩ አገራት ይላካል ነው የተባለው። ለአገራት ይከፋፈላል የተባለው የተቀረው 50 ሚሊየን ክትባት በተለያየ የምርት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ተጠቅሷል።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ እንዳሉት የትኞቹ አገራት ክትባቱን እንደሚያገኙ በቀጣይ ይገለጻል።

የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ተቆጣጣሪ እስካሁን ፍቃድ የሰጠው ለፋይዘር ባዮንቴክ፣ ለሞደርና እና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ነው።

እነዚህ ክትባቶች ለአገሪቱ ዜጎች በቂ ስለሚሆኑ ተጨማሪ የአስትራዜኒካ ክትባት እንደማያስፈልግ ተንታኞች ይናገራሉ።

እስካሁን በአሜሪካ ከ53 በመቶ በላይ የሚሆኑ አዋቂዎች የመጀመሪያ ዙር ክትባት አግኝተዋል።

የባይደን አስተዳደር ወደ 60 ሚሊየን የሚጠጋ ክትባት ለመለገስ ውሳኔ ማሳለፉ “የክትባት ዲፕሎማሲ” ሲሉ ተንታኞች መግለፃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።