ግብፅና ሱዳን በየጊዜው የሚፈጥሩት መሰናክል የኢትዮጵያን ህዝብ ከግድቡ ግንባታ ስኬት የሚያስቀር አለመሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 24 /2013 (ዋልታ) – ግብፅና ሱዳን በየጊዜው የሚፈጥሩት መሰናክል፣ ዛቻና ማስፈራሪያ የኢትዮጵያን ህዝብ ከጀመረው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ሊያስቀረው የሚችል አለመሆኑን የተለያዩ ባለሙያዎች ተናገሩ።
ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዳይሳካ የሚያደርጉት ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም መሰናክል የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ ሆኖ ግድቡን በፍጥነት እንዲያጠናቅቅ ብርታት ሆኗል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ ባለሙያዎችና የምክር ቤት አባላት እንደሚሉት የኢትዮጰያ ህዝብ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅን በጉጉት እየተጠባበቀ ይገኛል።
ከዛሬ አስር ዓመት በፊት የግድቡ መሰረተ ድንጋይ ሲጣል ጀምሮ አሁን እስከ ደረሰበት የግንባታ ደረጃ ህዝቡ በንቃት እየተከታተለና እየተሳተፈ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ባለፉት አስር ዓመታት በግድቡ ላይ ከውስጥም ከውጭም የሚመጡ ጫናዎችን በመቋቋም የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መካሄዱን አንስተዋል።
የውሃው ሙሌት ጊዜ ሲደርስ በተለይ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት በኢትዮጵያ ላይ መሰናክል፣ ዛቻና ማስፈራሪያም ጭምር ሲያደርሱ እንደነበር አስታውሰዋል።
የውሃ ጥናት ባለሙያው አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ እንደሚሉት ግድቡ እስከተገነባ ድረስ የውሃ ሙሌቱን መከልከል እንደማይቻል ግብጽም ሆነች ሱዳን ጠንቅቀው ያውቁታል ብለዋል።
በተለይ ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ ለማስተጓጎል ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንደሌለ ጠቅሰዋል።
ጉዳዩን ከልማት ባለፈ አለም አቀፍ አጀንዳ ለማድረግ የሚያሰሙት ጩኽት ጉዳዩን አለም አቀፋዊ የደህንነት ጉዳይ ለማድረግ ካላቸው ፍላጎት መሆኑን አብራርተዋል።
መምህርና ደራሲ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ በአባይ ወንዝ ጉዳይ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ከኢትዮጰያ ጋር የጀመሩት አለመግባባት የቅርብ ጊዜ ሳይሆን ከአጼ ዘረዓያቆብና ከአጼ ዳዊት ዘመነ መንግስት ጀምሮ የነበረ ነው ይላሉ።
‘’ጸሃይ ከተፈጠረች ሺህ ዘመናትን ብታስቆጥርም የሰው ልጅ ሰው ሰራሽ ሃይል መጠቀም የጀመረው በቅርቡ ነው’’ ያሉት ዲያቆን ዳንኤል አባይ መፍሰስ ከጀመረ ሺህ ዘመናት ቢያልፉም የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጅማሮ ቅርብ ነው ብለዋል።
‘’በህዳሴው ግድብ ላይ የሚራገቡ የተሳሳቱ መረጃዎችና ጩኽቶች ከኢትዮጵያ ህዝብ አቅም በታች ናቸው’’ ያሉት ዲያቆን ዳንኤል ህዝቡ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑ አያጠያይቅም።
ለዚህ ደግሞ ትልቁ ማሳያ ዛቻና ማስፈራራቶች ሳያግዱት ግንባታው እየተከናወነ መሆኑም ነው የገለጹት።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ታደሰ መሰሉ እንደሚሉትም የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ወደ ጎን በመተው የቅኝ ግዛት ውሎችን ለመተግበር ጥረት እያደረጉ ነው።
የኢትዮጰያ ህዝብ የቅኝ ግዛት ስነ-ልቦና ጫና የሌለበትና በራሱ ጥቅም የማይደራደር በመሆኑ የግድቡን ግንባታ አጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ በበርካታ ውጣ ውረዶችን ያለፈው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፍሬ የሚያፈራበት ጊዜ ላይ ደርሷል።
የኢትዮጵያ ህዝብም ከውስጥና ከውጪ የሚደርሱበትን ጫናዎች እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ግድቡ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል።
ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ ከሚያደርገው የገንዘብ፣ የጉልበትና የሀሳብ አስተዋጽኦ ባለፈ የህይወት መስዕዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም በመጠቆም።
የታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ እስካሁን እያንዳንዱ ዜጋ በሚችለው ሁሉ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ባለፉት አስር ዓመታትም ለግድቡ ግንባታ ከ15 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ታውቋል።