አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከተመድ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ጋር ተወያዩ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ፓርፋይት ኦናንጋ አንያንጋ ጋር ተወያዩ።

ውይይቱ ስለተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ በትግራይ ክልል በሁለት ካምፕ  የኤርትራ ስደተኞች ያሉበትን ሁኔታ ለመገንዘብ ያደረጉት ጉብኝት፣ የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ በክልሉ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ እየተደረገ ስላለው ርብርብ፣ የመልሶ ማቋቋም ሥራ፣ የህወሓት ጁንታ ያፈራረሳቸው መሰረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ፣ የክልሉ  ጊዜያዊ አስተዳደር እያደረገ ያለው ጥረትና ያለበት ውስንነት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህ ወቅትም አምባሳደር ሬድዋን ለ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በመጥቀስ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ ገለጻ ያደረጉላቸው ሲሆን፥ መንግስት ጉዳዩ በድርድርና በውይይት ብቻ እንደሚፈታ እምነት እንዳለውም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ በሁሉ ቦታ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጁንታው አባላትና አጋፋሪዎቹ መንግስት በክልሉ እያደረገው ያለውን የሰብአዊ እርዳታ አሳንሰው የማቅረብና ጉዳዮን ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ፣ በለጋሽ ድርጅቶችና በሌሎች  የሚነሱና የሚነዙት ሃሳቦችና ጥያቄዎች ዙሪያም ተወያይተዋል።

አያይዘውም የህወሓት ቡድን የህግ ማስከበር ዘመቻውን ቀጠናዊ ችግር ለማስመሰል የጎረቤት ሃገር ኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ውስጥ ገብተው በዘመቻው ላይ ተሳትፈዋል በሚል የውንጀላ ክስ ሲያቀርብ ቆይቷልም ብለዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል በቡድኑ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ወደ ነበሩበት እና የህዝቡን ኑሮ ወደ መደበኛ ለመመለስ ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ጨምረው ገልፀውላቸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ፓርፋይት ኦናንጋ አንያንጋ  በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት ለተባበሩት መንግስት ልዑካን ቡድን ለሥራ ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ጊዜ ለሚያደርግላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።

ሰብአዊ እርዳታን በትግራይ ክልል ተደራሽ ለማድረግ መንግስት እያደረ ያለውን ጥረት እንደሚያደንቁ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በሽግግር ላይ በመሆኑ መንግስታት በሽግግር የሚያልፉበት ያለመረጋጋትና  የደህንነት ስጋት ሊያጋጥም እንደሚችል የሚጠበቅ መሆኑን እንደሚረዱም ጠቅሰዋል።

የሰብአዊ ድጋፍን በማድረስ የኢትዮጵያ መንግሥትን በማገዝ ሊፈጠር የሚችልን ችግር ማስቀረት እንደሚቻል ተናግረዋል።

በኢትዮጵያና በሱዳን ያለው የድንበር ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የያዘው አቋም ትክክል መሆኑን በመጥቀስም፥ ትኩረት ያሻቸዋል ያሏቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ጥያቄ አቅርበዋል ።

አምባሳደር ሬድዋን ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት በትግራይ ክልል የሚደረግ ሁሉን አቀፍ ርብርብ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት ይሰራል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ  ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።