የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ከጂቡቲ፣ ናይሮቢ እና ዳካር የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደሮች ጋር በበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱም በውጭ ሀገራት ያሉ ሚሲዮኖች ሀብት በማፍራት የተሳለጠ የዲፕሎማሲያዊ ሥራ ማከናወን እና ሀገሪቱ በመደጋገፍ መርህ የምታገኛቸውን ጥቅሞች አሟጦ ለመጠቀም በተያዙ ሥራዎች ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል።
በዚህም በዳካር እየተገነባ ያለው የአምባሳደር መኖሪያ ግንባታ ሂደት፣ በጂቡቲ እየተገነባ ያለው የአምባሳደር መኖሪያና የዲፕሎማቶች መኖሪያ ቤት ህንፃ ግንባታ እድሳት እንዲሁም በናይሮቢ ለኤምባሲው ለሚገነባው ቢሮና የቢዝነስ ህንፃ ግንባታ ዝግጅት ተገምግሟል።
መጨረሻም ሚኒስትር ዴኤታዋ ሀብት ለማሰባሰብና በቀጣይ ሥራውን ማፋጠን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለአምባሳደሮች አቅጣጫ መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡