የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረበት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓል በሻንጋይ ተከበረ

የኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓል በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲና በሻንጋይ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት በጋራ በሻንጋይ ከተማ ተከበረ።

በበዓሉ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ በበየነ መረብ ተሳትፎ በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይ  በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉስልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ በሻንጋይ  ቆንስል ጄኔራል አቶ ወርቃለማሁ ደስታ እና የቻይና የተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች ተሳትፈው  የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ወይዘሮ ጽዮን ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ እና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ እና ግንኙነቱ ሁሉን አቀፍ መሆኑንም አንስተዋል።

ሁለቱ አገራት በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው መሆኑንና በአገራችን የውጭ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሳትፎ የቻይና ባለሀብቶች ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዙ ጠቅሰዋል።

አያይዘውም ይህን ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት የሚያደርጉትን  ከፍተኛ አስተዋጽዖ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪም አስተላልፈዋል።

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በበኩላቸው በቻይና የሚገኙ ሚስዮኖች በተለያዩ ሥነ-ስርዓቶች ታሪካዊ በዓሉን እያከበሩ እንደሚገኙ ገልፀው፣ በቀጣዩ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ቻይና አጋርነቷን አጠናክራ እንድምትቀጥል እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ በዓመቱ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የቻይና መንግስት እና የቢዝነስ ማህበረሰብ ለታዳጊ አገሮች በተለይም ለኢትዮጵያ ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የቻይና የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶች፣ የንግድ ማህበረሰብ፣ ምሁራን፣ አርቲስቶች ጋዜጠኞች፣ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እና የዲያስፖራ አባላት እንዲሁም፤ በሻንሃይ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትም የተሳተፉ ሲሆን፣ ከ17 ሺ በላይ ተመልካቾች ፕሮግራሙን በበየነ መረብ በቀጥታ መከታተላቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።