አምባሳደር ይበልጣል በሱዳን ከኖርዌይ አምባሳደር ጋር ተወያዩ

በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን የኖርዌይ አምባሳደር ቴሬዝ ሎክን ህዜል ጋር ተወያይተዋል።

በወቅቱም በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።

ከዚህ ጋር በተያይዘ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝን እንዲሁም የኢትዮጵያንና የሱዳንን ድንበር እና በቀጠናው የሚስተዋሉ ጉዳዮችን በተመለከተ አምባሳደሯ ላነሷቸው ጥያቄዎች ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚሁ መሰረት በትግራይ ክልል ከሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትና ሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የተዛቡ አስተያየቶች መንግስት በአካባቢው ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ በመሆናቸው ለትግራይ ሕዝብም ሆነ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያውያን እቆረቆራለሁ የሚል አካል ካለ የመንግስትን ጥረት መደገፍ እንደሚገባ አምባሳደር ይበልጣል አስረድተዋል፡፡

አምባሳደሩ አያይዘውም የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ችግር የሚፈቱባቸው መንገዶች በግልፅ በስምምነት የተቀመጡ በመሆኑ በዚሁ መሰረት ዘላቂ ሰላም በሁለቱ ሀገራት እና በቀጠናው በሚያመጣ መልኩ መፍታት እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ከሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።