አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ ለተመድ ዋና ፀሀፊ ልዩ ተወካይ በወቅታዊ የኢትዮጵያና የቀጠናው ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሰጡ

መጋቢት 28/2013 (ዋልታ) – በሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ ለተባበበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሀፊ ልዩ ተወካይና በሱዳን የተመድ የተቀናጀ የሽግግር ድጋፍ ተልዕኮ ሃላፊ ቮልኬር ፐርተኸስ በወቅታዊ የኢትዮጵያና የቀጠናው ጉዳይ ላይ ማብራርያ ሰጡ።
በውይይታቸውም አምባሳደር አእምሮ ኢትዮጵያ በሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር ላይ ያሉ ጉዳዮችን በተቀናጀና ህጋዊ የሆኑ ዶክመንቶች በመያዝ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ ሃላፊነት በተሞላበትና ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሙሌት እንደምታከናውንና የድርድሩም ሂደት ይህንን በጠበቀ መልኩ እንዲካሄድ በሃላፊነት እየሰራች ነው ብለዋል።
በተጨማሪም አምባሳደሩ በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ እየተከናወኑ ስለሚገኙ ሰብአዊ ድጋፎችና የሚዲያ ተቋማት እንቅስቃሴ ገለጻ ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።