አቶ ደመቀ መኮንን ለኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ግንቦት 04/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለመላው የሀገሪቱ ሙስሊሞች ለ1442ኛ ጊዜ ለሚከበረው የኢድ አልፈጥር በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
ታላቁ የረመዳን ፆም በአማኞቹ ዘንድ ልዩ ሀይማኖታዊ ትርጉም ያለው ነው ያሉት አቶ ደመቀ፣ በአንድ ወር የፆም ፀሎት ጊዜ ከዕምነቱ ውጪ ያሉ ወገኖች ጋር አንድነትን ይበልጥ ለማጥበቅ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ እንደነበር ገልጸዋል።
አያይዘውም በልዩነቶች ላይ ቆሞ ከመሳሳብ ይልቅ አንድነትን በሚያፀኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ዘላቂ ሰላም እውን ማድረግ ቀዳሚው ሃላፊነታችን ነው ብለዋል፡፡
የለውጥ ጉዞው በልዩነቶች ላይ ቆሞ ከመሳሳብ ይልቅ፤ አንድነታችንን በሚያፀኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ተጎጂ ወገኖችን የመደገፍና ዘላቂ ሰላም እውን ማድረግ ቀዳሚው ኃላፊነታችን ይሆናል ሲሉ አቶ ደመቀ መኮንን ገልፀዋል።
“መልካም አጋጣሚዎችን ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት በተዘጋጁ የኢፍጠር መርሃ ግብሮች ላይ ልዩነቶቻችን ሳይገድቡን ማዕድ የተጋራንባቸው መድረኮች የአብሮነታችን ውሃልክ ትክክለኛ ማሳያዎች ነበሩ” በማለትም ጠቅሰዋል።
“በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተሰባስበን አንድነታችንን ይበልጥ የሚያጠብቁ እና የሚያደምቁ መርሃ ግብሮችን ሃገራዊ መሰረት እና ይዘት እንዲኖራቸው የበለጠ መስራት ይጠበቅብናል” ብለዋል በመልካም ምኞት መልዕክታቸው።
ባለፉት ጊዜያት በዜጎች ላይ ያጋጠሙ አሳዛኝ ጥፋቶች እንዳይደገሙ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ከውስጥ እና ከውጭ ከገጠመን ፈተና በጥበብ ለመሻገር በፅናት መረባረብ እንደሚገባም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በተለየ የዜጎቿ ደህንነት እንዲጠበቅ፣ አንድነታቸው እንዲጠናከር እና እንዲደምቅ የሻተችበት ወቅት ላይ እንገኛለንም ብለዋል።
የለውጥ ጉዞው በልዩነቶች ላይ ቆሞ ከመሳሳብ ይልቅ፤ አንድነታችንን በሚያፀኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ተጎጂ ወገኖችን የመደገፍና ዘላቂ ሰላም እውን ማድረግ ቀዳሚው ኃላፊነታችን ይሆናል በማለት ነው የገለጹት።
አቶ ደመቀ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መልዕክት “በታላቁ የረመዳን ወር ከአንድነታችን የሚቀዳው መደጋገፍ፣ መተሳሰብ እና መረዳዳት ኢትዮጵያዊ መሰረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ ለማለት እወዳለሁ” ብለዋል።