አየር መንገዱ ” የኤርፖርት ሲቲ” ግንባታ በአራት ዓመታት ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለማ ያደቻ

ታህሣሥ 2/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየጨመረ የመጣውን የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት የቢሾፍቱ የጀመረውን ” የኤርፖርት ሲቲ” ግንባታ በአራት ዓመታት ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

በአሁን ጊዜ “ኤርፖርት ሲቲ” ግንባታ ለማስጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።

የአየር መንገዱ የንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለማ ያደቻ እንዳሉት አየር መንገዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 በዓለም ስመ-ጥር ከሆኑ 20 አየር መንገዶች አንዱ የመሆን ራዕይ ይዞ እየሰራ ነው።

ይህን ራዕይ ለማሳካትም አየር መንገዱ ጠንካራ የሥራ ባህል እንዳለውና አዳዲስ አሠራሮችን በመተግበር ዓመታዊ ዕድገቱን በአማካኝ ከ20 እስከ 25 በመቶ ማድረስ መቻሉንም አንስተዋል።

አየር መንገዱ በተያዘው ዓመት 84 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ያቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የ25 አውሮፕላኖች ግዥ በመፈፀሙ ለመረከብ እየጠበቀ መሆኑን አንስተዋል።

የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አሁን ባለው ሁኔታ በዓመት 25 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ለማ ተናግረዋል።

በ2015 አየር መንገዱ 14 ሚሊየን መንገደኞችን ያስተናገደ ሲሆን፤ በተያዘው ዓመት ደግሞ 18 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

አየር መንገዱ እያስመዘገበ ያለውን ፈጣን ዕድገት ለማስተናገድም በቢሾፍቱ ከተማ ተለዋጭ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያና የኤርፖርት ከተማ ለመገንባት ከአዋጭነት ጥናት ጀምሮ በቂ ዝግጅቶች እያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።
“የኤርፖርት ሲቲ” ፕሮጀክት በአጠቃላይ 5 ቢሊየን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን፣ በዓመት 100 ሚሊየን መንገደኞችን ያስተናግዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።

በኦሮሚያ ክልል ከቢሾፍቱ ከተማ ጥቂት ወጣ ባለ ሥፍራ ላይ እንደሚገነባ የተገለጸው ይህ ፕሮጀክት፤ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ ከቀረጥ ነፃ የግብይት ሥፍራና የካርጎ ሎጂስቲክስ ማዕከል እንደሚኖረውም ነው የተገለጸ ሲሆን በአሁን ጊዜ ግንባታውን ለመጀመር የአዋጭነት ጥናት በማጠናቀቅ ዓለም አቀፍ ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን እያሳየ ያለውን ፈጣን ዕድገትና ትርፋማነት ግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የአየር መንገዱን ካፒታል ከነበረበት 100 ቢሊየን ብር ወደ 300 ቢሊየን ብር ከፍ እንዲል አድርጓል።