አገልግሎቱ የክፍያ ተመን መመሪያን በአስቸኳይ እንዲያጸድቅ እና ተሰብሳቢ ሂሳብ በሦስት ወራት ጊዜ እንዲሰበስብ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

ክርስቲያን ታደለ

ግንቦት 23/2015 (ዋልታ) የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የክፍያ ተመን መመሪያን በአስቸኳይ እንዲያጸድቅ እና ተሰብሳቢ ሂሳብ በሦስት ወራት ጊዜ እንዲሰበስብ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የ2013 ዓ.ም የኦዲት ግኝትን ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክርስቲያን ታደለ አገልግሎቱ ባልጸደቀ ህግ ሂሳብ መሰብሰቡና ክፍያ መፈጸሙ ትክክል አለመሆኑን ጠቁመዋል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሳይፈቀድ የፈተና ማስፈጸሚያ የክፍለ ጊዜ ክፍያ በሚል ከተፈታኞች ምዝገባ ጀምሮ እስከ ፈተና አሰጣጥ ድረስ ለተሳተፉ ከህግ ውጪ የተፈጸመው ክፍያ አግባብነት እንደሌለው ተናግረው የገንዘብ አሰባሰብ ስርዓቱ በህግና በመመሪያ ሊከናወን እንደሚገባውም አሳስበዋል።

በደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ክፍያዎች ላይ በተደረገ ኦዲት አገልግሎቱ ባልተፈቀደ መንገድ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ያለመመሪያ ክፍያ መፈጸሙ መረጋገጡም በሪፖርቱ ተጠቁሟል።

አገልግሎቱ ባልጸደቀ ህግ የሚሰበስበው እና የሚከፍለው ሂሳብ ከስልጣኑና ከህግ ውጭ በመሆኑ የትምህርት ሚኒስቴር በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቅ ያለበትን የክፍያ ተመን በአስቸኳይ የሚጸድቅበት ሁኔታ እንዲያመቻች ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ሊፈጥር የሚችለውን ችግር ታሳቢ በማድረግ በፍጥነት ሊፈጸም እንደሚገባውም ነው የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ያሳሰቡት። ፈተና የሚሰጥበት ሐምሌ ወር ሳይደርስ መመሪያው መጽደቅ እንዳለበትና አገልግሎቱ የበጀት ፍላጎትና አጠቃቀሙን በእቅድ በመምራት ሊያሻሽል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የ76 ዓመታት የአገልግሎት ዘመን ያለው ተቋም በኦዲት አሰራር ለሌሎች አብነት መሆን እንደሚገባ ገልጸው አገልግሎቱ የሚታዩበትን ችግሮች በዘላቂነት በመፍታት ተቋሙን ማስቀጠል የሚችል የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ምሳሌ መሆን እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ሳይወራረድ እየተንከባለለ የቆየ ሂሳብ ሊስተካከል እንደሚገባውና ተሰብሳቢ ሂሳብን በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ መሰብሰብ እንደሚገባውም አቶ ክርስቲያን ተናግረዋል።

የፋይናንስ ህጎችና ድንጋጌዎችን በጣሰ መንገድ ለጽዳትና ለጥበቃ ሰራተኞች ሲፈጸም የነበረ ክፍያ እንዲቆም መደረጉ ተገቢ ቢሆንም ህግን ያልተከተለ ክፍያ ተመላሽ ሊደረግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው ተሰብሳቢ ሂሳብ በ2014 ዓ.ም 54 ሚሊየን ብር እንደነበር አስታውሰዋል።

ከመንግስት ካዝና የወጣ ገንዘብ መሰብሰብ እንዳለበት አሳስበው ሰነድ ያልቀረበለት ቀርቦ መወራረድ ይጠበቅበታል፣ መመለስ ያለበትም ሊመለስ ይገባዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። መሰብሰብ የማይችል ከሆነ ደግሞ ተገቢው ሰነድ ስልጣን ላለው አካል ቀርቦ ሊሰረዝ እንደሚገባው አመላክተዋል።

‹‹ለጽዳትና ለጥበቃ የተከፈለው ገንዘብ ችግሩ የአገልግሎቱ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ተቋማት የሚከሰት በመሆኑ የችግሩን ተደጋጋሚነት ተመልክቶና ተገቢ ጥናት ተጠንቶ ችግሩ ከመሰረቱ መፈታት አለበት›› ብለዋል።

‹‹እነዚህ አካላት ማግኘት ያለባቸውን ማግኘት አለባቸው። ህግ እየተጣሰ ያለው ማግኘት የሚገባቸውን ስላለገኙ ነው›› ያሉት ዋና ኦዲተር መሰረት ችግሩን አጥንቶ ለዘለቄታው መፍታት ይገባል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተፈራ ፈይሳ ባልጸደቀ መመሪያ ለፈታኞች ክፍያ መፈጸሙ ትክክል አለመሆኑን እናምናለን ብለዋል። ነገር ግን ስራ መስራት ባለመቻላችን ከአቅም በላይ በሆነ መንገድ የተፈጸመ ነው በማለት ያልተወራረደ ሂሳብን ለማስተካከል ሰራተኞች መቀጠራቸውንም አመልክተዋል።