የአፍሪካ የስራ ዕድል ፈጠራ ጉባኤ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው

ግንቦት 21/2015 (ዋልታ) የአፍሪካ የስራ እድል ፈጠራ ጉባኤ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 2/2015 በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

የፎረሙ ቅድመ ስብሰባ ከዲፕሎማቲክ፣ ዓለም አቀፋ ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተገኙበት በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተከናውኗል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በአፍሪካ እያደገ የመጣውን አምራች የሰው ኃይል ለአፍሪካ የምጣኔ ሀብት እድገት እንደ እድል መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንና የብሔራዊ የስራ ዕድል ፈጠራ እቅድ ተግባራዊ ማድረጉ በማሳያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

በአፍሪካ የምጣኔ ሀብት ውህደትን ለማምጣት እየተሰራ እንዳለው ሁሉ በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ በኩልም በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

እቅዶችን በጋራ በማውጣትና በመተግበር በኩል በቀጣይ ሐምሌ የሚካሄደው አህጉራዊ የስራ እድል ፈጠራ ጉባኤ ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 2/2015 ለሚካሄደው አህጉራዊ የስራ ዕድል ፈጠራ ጉባኤ ስኬታማነት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸው የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሐፉ አንቶኒዮ ፔድሮ በበኩላቸው በአፍሪካ በ2035 አምራች የሰው ኃይል ቁጥር 450 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በመሆኑም አገራት በፍጥነት እያደገ ለመጣው የስራ ፈላጊዎች ቁጥር ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ በአፍሪካ ያሉ የስራ እድል ፈጠራ አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና አንዱ ትልቅ እድል በመሆኑ መንግስታት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።