አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ የምርጫ ቅድመ-ዝግጅትን በተመለከተ ከአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢዎች ጋር ተወያዩ

አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ

ሚያዝያ 26/2013 (ዋልታ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ የ6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ-ዝግጅት አስመልከቶ ከአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢዎች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡

ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሳተፉበት መንገድ የምርጫ ሕጉ መሻሻሉንና የምርጫ ቦርድ አባላት መመረጣቸውን አፈ ጉባኤው  ለታዛቢዎቹ አብራርተውላቸዋል፡፡

ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲከናወን ለማድረግ የምርጫ ቁሳቁስ ወደየምርጫ ጣቢያው እንደተጓጓዙ የጠቀሱት አፈ ጉባኤው፣ በምርጫው ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ሕጋዊ አሰራሮችና የጸጥታ አደረጃጀቶች እንደተዘረጉም ተናግረዋል፡፡

በጸጥታ ስጋት ምክንያት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተራዝሞ የነበረው የመራጮች ምዝገባ በአሁኑ ጊዜ ከሞላ ጎደል መጠናቀቁን የተናገሩት አቶ ታገሠ፣ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በተደረገው ዝግጅት ዙሪያም ታዛቢ ቡድኑ በቂ መረጃ ማግኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

ሴቶች መራጭ ብቻ ሳይሆኑ ተመራጭም እንዲሆኑ በማድረግ በምርጫው የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አፈ ጉባኤው፣ በአሁኑ ወቅት በአመራር ሰጭነት የሴቶች ተሳትፎ 50 በመቶ መሆኑን መጥቀሳቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡