ሱዳን የቤንሻንጉል መሬት የእኔ ነው ማለቷ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፃረር ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ሚያዝያ 26/2013 (ዋልታ) – የሱዳን መንግስት የቤንሻንጉል መሬት የእኔ ነው ማለቷ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፃረር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

ሚኒስቴሩ በሳምንታዊ መግለጫው እንዳስታወቀው የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን መሬት ያለ አግባብ በመያዝ አርሶ አደሮችን ማፈናቀሉ ሳያንሰው ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ የቤንሻንጉል መሬት ይገባኛል ማለቱ እጅግ አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡

የሚኒስቴሬ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ የቤንሻንጉል ጉዳይ ከህዳሴ ግድብና ከድንበር ጉዳይ ጋር የሚገናኝ አይደለም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

የሱዳን መንግስት በአሁኑ ሰዓት የግድቡን ጉዳይ ከድንበር ጉዳይ ጋር የሚያምታታበት አካሄድ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለውም ቃል አቀባዩ አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

ኢትዮጵያ እስከ አሁን ያሳየችው ትዕግስት ለጎረቤት አገራትና ህዝቦች ያላትን ክብር የሚያሳይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የሱዳን መንግስት ባወጣው መግለጫ ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግስት ከሰዓታት በኋላ ዝርዝር መግለጫ የሚያወጣ መሆኑንም ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡