አየር መንገዱ 5 ተጨማሪ የሀገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ ነው

መጋቢት 11/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ 5 ተጨማሪ የሀገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት፤አየር መንገዱ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ለማስፋት እየሰራ ይገኛል።

አየር መንገዱ የሚያበራቸውን አውሮፕላኖች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ 136 ዓለም አቀፍ እንዲሁም 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች እንዳሉት ገልጸዋል።

ኤርፖርቶቹ የሚገነቡት ሚዛን ቴፒ አማን፣ ነጌሌ ቦረና፣ ያቤሎ፣ ጎሬ መቱ እና ደብረ ማርቆስ መሆናቸውን ገልጸው፤ አራቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው

ይህም በሀገር ውስጥ ያሉ ደንበኞች ፍላጎትን ተከትሎ የሚተገበር ሲሆን በቀጣይም ሌሎች መዳረሻዎች ጥናት ላይ በተመሠረተ መልኩ ግንባታ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ጉዳት የደረሰባቸው የአክሱም እና ቀብሪደሃር ኤርፖርቶች እድሳት እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡም ዋና ሥራ አስፈጻሚው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.ኤ.አ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።