ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል የሚያደርጉትን ጥረት ለማክሸፍ በጋራ መቆም ያስፈልጋል – የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – ግብጽና ሱዳን በተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያን ሰላም በማወክ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል የሚያደርጉትን ጥረት ለማክሸፍ ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመቆም ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲከታተሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ አመራሮች ሁለቱ አገሮች የኢትዮጵያን ሰላም በተለያዩ አጋጣሚዎች በማወክ የግድቡ ግንባታና ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አማካሪ ኢንጂነር ግደይ ዘርዓጽኦን ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳታከናውን ሲሰሩ የነበሩ አገሮች ዛሬም ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ በጋራ በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አገሮቹ በተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያን ሰላም በማወክ የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት እንዲፈጠርና ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ኢንጂነር ግደይ አብራርተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ በተጠናከረ መልኩ በጋራ በመቆም አንድነታቸውን በማስጠበቅና ሰላማቸውን በማረጋገጥ ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር ያሬድ ተሾመ በበኩላቸው፣ ሁለተኛውን ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት በስኬት በማከናወን የተያዘውን እቅድ ማሳካት የአገሪቷን ሉዓላዊነትም ማስከበር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ዶክተር ያሬድ አክለውም የግድቡ ጉዳይ የኢትዮጵያውያን የጋራ ትልም፣ የጋራ ስኬትና የጋራ ግብ በመሆኑ ከፖለቲካ ልዩነት በመውጣት ለጋራ አጀንዳ በጋራ መቆም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው፣ ግብጽና ሱዳን የህዝባቸውን ጥያቄ ላለመመለስ የህዳሴ ግድብን ግንባታ ለፖለቲካ ፍጆታቸው እያዋሉት መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለቱ አገሮች ግድቡን የውስጥ ፖለቲካ ችግራቸው መፍትሄ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

“አገሮቹ በኢትዮጵያና በህዳሴ ግድቡ ውሃ ሙሌት ጉዳይ ከመግባት ተቆጥበው የራሳቸውን የቤት ስራ መስራት አለባቸው” ብለዋል፡፡

በግድቡ ግንባታ ጉዳይ ኢትዮጵያዊያን ያለልዩነት በጋራ መቆም አለባቸው ሲሉም ጠይቀዋል።