አፕል ከ2019 በኋላ ከፍተኛ የሽያጭ ማሽቆልቆል እንዳጋጠመ ገለጸ

አፕል

ጥር 26/2015 (ዋልታ) የአፕል ኩባንያ ከ2019 ወዲህ ከፍተኛ የተባለ የምርት ሽያጭ ማሽቆልቆል እንዳጋጠመው አስታወቀ፡፡

እ.ኤ.አ በ2022 መጨረሻ 3 ወራት ብቻ የአይፎን ስልክ ሽያጭ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ5 በመቶ ቅናሽ እንዳሳዬም ነው ኩባንያው ያስታወቀው፡፡ ይህም ከ2019 ወዲህ ከፍተኛውና ከተጠበቀው የከፋ ቅናሽ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

ለዚህም እንደ ምክንያትንት የቀረበው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በቻይና የፈጠረው የግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የዶላር የመግዛት አቅም መጨመር እና በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

የአፕል ምርት ሽያጭ የቀነሰው በመላው ዓለም ሲሆን አይፎን በ8 ከመቶ እና ማክ ኮምፒውተሮች ደግሞ 29 ከመቶ መቀነሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በዚህም ከአፕል ኩባንያ አጠቃላይ ትርፍ 13 ከመቶ ወይም 30 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል ነው የተባለው፡፡

ነገር ግን የኩባንያው ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ምርቶቹ አፕል ፔይ እና አፕል ዜና የኩባንያውን እድገት ሊያሻሽሉት እንደሚችሉ የኩባንያው ኃላፊዎች መናገራቸውን ዘገባው አመላክቷል፡፡