ኢትዮጵያና ስዊድን ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ትስስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከስዊድኑ የአለም ዓቀፍ የልማት ትብብር ምክትል ሚኒስትር ፔር ኡልሰን ፍሪዝ ጋር ተወያይተዋል።

በነበራቸው የስልክ ቆይታ በሃገራችን ሰሜናዊ ክፍል የህግ ማስከበር ሂደት ውስጥ ከመገባቱ አስቀድሞ ሰላምን በስልጡን ምክክር ለማስፈን የተሄደበትን ረጅም ርቀት በዝርዝር አስረድተዋል።

በተጨማሪም በህግ ማስከበር ሂደቱ ወቅት ሰላማዊ ዜጎቻችን ጉዳት እንዳይደርስባቸው በከፍተኛ ጥንቃቄ መካሄዱን ተናግረዋል።

የስዊድኑ ምክትል ሚኒስትርም በበኩላቸው በሁለቱ ሃገራት መካከል የቆየው የእህታማማችነት ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ባለው ሁኔታ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ የማቋቋምና መሰረተ ልማትን መልሶ የመገንባት ርብርብን ለመደገፍ ከኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጎን መሆናቸውን አረጋግጠዋል።