ኢትዮጵያና ቻይና የ1.22 ቢሊዮን ብር የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት ተፈራራሙ

የካቲት 8/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያና ቻይና ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት መለዋወጫ የሚውል የ1.22 ቢሊዮን ብር የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት ተፈራራሙ፡፡

በፋይናንስ ድጋፉ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት 5 ሲስተሞች የሚውሉ 573 ዓይነት የመለዋወጫ እቃዎች የሚያሟሉ ሲሆን ይህም የመለዋወጫ ድጋፍ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ድርጅት ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው ተመልክቷል፡፡

ይህ የድጋፍ ስምምነት በቻይና እና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል ከሁለት ዓመት በፊት በተፈረመው የኢኮኖሚ እና የቴክኒክ ትብብር ስምምነት መሰረት የተከናወነ መሆኑም ታውቋል፡፡

ስምምነቱን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሺዴ እና የቻይናን መንግስት በመወከል በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛሆ ዚዩሀን መፈራረማቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡