ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ድኅረ ኮቪድ-19 ኢኮኖሚው በሚያገግምበት ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አካሄዱ

ግንቦት 10 /2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ድኅረ ኮቪድ 19 ኢኮኖሚው በሚያገግምበት ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማካሄዳቸው ተገለፀ።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴና የፈረንሳይ ግምጃ ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል ኢማኑኤል ሞውሊን ከኮቪድ 19 በኋላ ኢኮኖሚው በሚያገግምበት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት ወቅቱን በጠበቀና ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ባለፉት አስር ዓመታት ለአፍሪካ አገራት የተደረጉ የፋይናንስ ድጋፎች ያስገኙት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዲቀጥል የፋይናንስ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
ዳይሬክተር ጄነራሉ በበኩላቸው በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ አገራት ካጋጠሟቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ስለሚያገግሙበት የብድር ማቅለያ የጋራ ማዕቀፍ ገለጻ አድርገዋል።
አገራቱ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበት የፋይናንስና ሌሎች መስኮች ላይ ለመስራት ስምምነት የተደረሰ ሲሆን በተለይም የአፍሪካ አገራት የልማት ግቦቻቸው እንዲሳካ የፈጠራ ፋይናንስ መፍትሄዎች አስፈላጊነት ላይ መስራት እንደሚገባ መገለጹን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።