የፖስታ አገልግሎት የዲጂታል ፍኖተ ካርታ ወደ ተግባር ሊገባ ነው

ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – በጀርመን መንግስት ድጋፍ የተደረገለት የፖስታ አገልግሎት የዲጂታል ፍኖተ ካርታ ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያን ፖስታ አገልግሎት ለማዘመን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሀመድ፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሃና አረአያስላሴና የጀርመን የኢኮኖሚ ጉዳዮችና ኢነርጂ ሚኒስቴርን በመወከል በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ቀዳሚ ፀሃፊ ሆልዝፉስ ካሌ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ፈርመዋል።
የፖስታ አገልግሎቱን ለማዘመን በተደረገ ጥናት መሰረት የኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎትን በዲጂታል መንገድ ለማዘመን የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስችል ውይይት እየተደረገ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሀመድ የጀርመን መንግስት የኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎትን ለማዘመን እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሚደገፉ አገልግሎቶችን መስጠት አንዱ ስራ መሆኑን ገልጸው፣ “የፖስታ አገልግሎት ማዘመን ለኢ-ኮሜርስ አገግልግሎት ጅማሮ መደላድል ይፈጥራል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሃና አረአያስላሴ የፖስታ ዲጂታል ፍኖተ ካርታው በፍጥነት ወደ ትግበራ እንዲገባ የጀርመን መንግስት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ቀዳሚ ፀሃፊ ሆልዝፉስ ካሌ ከፍኖተ ካርታው ትግበራ በተጨማሪ በቀጣይ በተለያይዩ ጉዳዮች በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የፖስታ አገልግሎት መዘመን የፖስታ እና ጥቅል እቃዎችን ማድረስ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላትና በማዘመን ወደ ኢ-ኮሜርስ አገልግሎት ለሚደረገው ጉዞ አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።