ኢትዮጵያ ለስደተኞች መጠለያ በመሆን እየፈጸመች ላለችው በጎ ተግባር ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን – ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት

መጋቢት 28/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ወደ ግዛቷ ለሚመጡ ስደተኞች መጠለያ በመሆን እየፈጸመች ላለችው በጎ ተግባር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ገለጸ።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች ወደ ግዛቷ የሚገቡ የጎረቤት ሀገራት ዜጎችን ተቀብላ በማስተናገድ ትታወቃለች።
በቅርቡም በሶማሌላንድ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ100 ሺህ የማያንሱ የአካባቢው ዜጎች ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ በስደት ገብተዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዓለም አቀፍ ፍልሰት ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ሞሐመድ አብዲከር፤ ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ አገር ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ የምትታወቅ መሆኗን በአጽእኖት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስደተኞች አያያዝ እያሳየች ያለችው መልካም ተግባር የሚያስመሰግናት መሆኑንም ገልጸዋል።
ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እያደረገች ላለው የሰብአዊ ዕርዳታ እና የመጠለያ አቅርቦት ድርጅቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ድርጅቱ ኢትዮጵያ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ በድንበር አስተዳደር ላይ ለምታከናውናቸው ተግባራት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በፍልሰት ዙሪያ ያላትን ትብብር አድንቀው፤ ድርጅቱ ኢትዮጵያ ያላትን የመሪነት ሚና ለመደገፍም ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ተጠልለው ለሚገኙ እና ሰብአዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ፍልሰተኞች ለጋሽ ድርጅቶች ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።