ኢትዮጵያ ከመጪው ትውልድ የተዋስናት አገር ናት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ሚያዝያ 29/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ከአባቶቻችን የወረስናት አገር ሳትሆን ከናንተ ወይንም ከመጪው ትውልድ የተዋስናት አገር ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

“ቃል፤ ተግባር፤ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ ለስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ እና የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት ተጠናቅቋል።

በመዝጊያ መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትውልዱ የሚያነብ፣ ነገሮችን በትኩረት የሚያይ እና የሚያዳምጥ ሲሆን አሁን ካለችው የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን ብለዋል፡፡

በዐውደ ርዕዩ የመዝጊያ መርኃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጻፈው የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ላይ ያተኮረ ውይይት በተማሪዎች የተካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተማሪዎቹ መልዕክት እና ምስጋና ተቀብለዋል፡፡

ተማሪዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትውልዱን የሚቀርፅ እንዲህ ያለ መፍትሔ እና አቅጣጫ ጠቋሚ መጽሐፍ ስላበረከቱልን እናመሰግናለን ብለዋቸዋል፡፡

አክለውም ምቹ የትምህርት ሥርዓት እና ከባቢ እንዲፈጠርላቸውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ተማሪዎቹ እኛ የምንረከባት የነገይቱ ኢትዮጵያ በዕውቀት የተገነባች ጠንካራ አገር እንደምትሆን በመጽሐፉ ላይ በሚገባ መቀመጡንም አመልክተዋል፡፡

አገር በቀል ዕውቀት፣ ባህል እና ታሪክን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ የሚያምን እና የሚታመን፣ በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድን ለመፍጠር እየተሰሩ ያሉ አበረታች ስራዎችንም ተማሪዎቹ አንስተዋል፡፡

በመጽሐፉ ላይ የመደመር ትውልድ ተብሎ የተገለጸው እነሱ የሚወክሉት ትውልድ የኢትዮጵያ ተስፋ መሆን እንዳለበት የገለጹት ተማሪዎቹ አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ ችግሮችን በውይይት በመቅረፍ የሚያምን፣ ጠንካራ የትምህርት ሥርዓትን በመፍጠር የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማሻገር የሚጥር እንዲሆን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ተማሪዎቹ ከመደመር ትውልድ መፅሐፍ ላይ የተመረጡ ጽሑፎችንም ለታዳሚያን አንብበዋል፡፡

“ቃል፤ ተግባር፤ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ ከሚያዝያ 24 እስከ 29/2015 ዓ.ም የቆየው ዐውደ ርዕይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአመራርነት ዘመናቸው ለህዝብ ያቀረቧቸው የህትመት ውጤቶች የተዋወቁበት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባለፉት ዓመታት የተፃፉ ሥራዎች የተገመገሙበት እና የመፅሐፍ ሽያጮች የተከወኑበት እንዲሁም የንባብ ባህልን ለማሳደግ የሚያግዙ ውይይቶች የተካሄዱበት ሆኖ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።

በሳሙኤል ሓጎስ