ጠ/ሚ ዐቢይ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በቂ ምርት በጥራት ማቅረብ እንደሚገባ ገለጹ

ሚያዝያ 29/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በቂ ምርት በጥራት ማቅረብ እንደሚገባ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የምርምር ፈጠራዎች ዐውደ ርዕይን በዛሬው ዕለት ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ከግብርና ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ገልጸው ለዚህም ግብርናን እንዴት አዘምነንና አሳድገን ተፈላጊውን ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል ለሚለው ጥያቄ ዐውደ ርዕዩ በበቂ ሁኔታ የሚያሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የግብርና ውጤቶቻችን በዓለም አቀፍ ገበያ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስገኙ ምርታማነትን በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በምርምር ስራዎች አጠናክሮ መደገፍና መተግበር እንደሚገባም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በስንዴ፣ በማር እንዲሁም በቡና ምርታማነት ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ገበያ የሚፈለገውን ገቢ አላስገኙም ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በቂ ምርት በጥራት ማቅረብ እንደሚገባ ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምርታማነቱን በተለያዩ ሰብሎች አጠናክሮ ለማስቀጠል አውደ ርዕዩ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ጠቁመዋል።

በደረሰ አማረ