በአልጀርስ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ትላንት ከሬዲዮ አልጄሪያ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ በግዛቷ የምታካሂደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ሉዓላዊ መብቷ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በትግራይ ክልል የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ በአጭር ጊዜ በድል መጠናቀቁና ቀጣዩ ሥራ ተፈላጊ የሆኑትን የአጥፊውን የጁንታ አባላት በቁጥጥር ሥር አውሎ ለህግ የማቅረብ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በአጥፊው ቡድን የተከሰተውን ግጭት ቀጠናዊና ዓለም ዓቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በኤርትራ ላይ ሮኬት በመተኮስ የተደረገው እኩይ እንቅስቃሴም የታለመለትን ዓላማ ሳያሳካ መክሸፉን አምባሳደሩ አብራርተዋል፡፡
የአፍሪካ ኀብረትን ጨምሮ በዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች በኩል የቀረቡ የውይይት ጥሪዎች ቢኖሩም መንግሥት በውስጥ ጉዳዩ ሕግንና ሥርዓትን የማስከበር ሙሉ አቅም ያለው መሆኑንና በዚህ ወቅት ከወንጀለኞች ጋር መደራደር ሳይሆን ለሕግ የማቅረብ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም ገልፀዋል፡፡
በክልሉ በቀጣይ የሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋምና የሰብዓዊ ዕርዳታ ጉዳዮች ዙሪያ በክልሉ ከተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን አምባሳደር ነብያት መግለጻቸውን አልጀርስ የኢፌዲሪ ኤምባሲን ዋቢ እድርጎ ኢዜአ ዘግቧል።