ጥቅምት 7/2014 (ዋልታ) “ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች በራሷ አቅም ከመፍታት የሚያግዳት መሰናክል የለም” ሲሉ የጋምቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማመዱ ታንጋራ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
የ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ተሳታፊዎች መካከል የሆኑት የጋምቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማመዱ በአዲስ አበባ እንጦጦ ፓርክን ጉብኝተዋል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ኢትዮጵያ ችግሮቿን በራሷ አቅም ከመፍታት የሚያግዳት መሰናክል የለም” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የነበረውን የቆየ ችግር የፈታችበትን መንገድ በማሳያነት ጠቅሰው የራሷን ችግር የማትፈታበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም ነው ያሉት።
የአፍሪካ አገራት ያሉባቸውን ችግሮች በራሳቸው የመፍታት አቅማቸውን ሊያዳብሩ ይገባል ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ሌሎች በእኛ ጉዳይ ከእኛ በልጠው ስለራሳችን ሊነግሩን አይችሉም” ብለዋል።
በአፍሪካ ጉዳይ ከአፍሪካዊያን በላይ መፍትሔ የሚያመጣ አካል ሊኖር አይችልም የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረው “አፍሪካን ለመለወጥ ቆርጠው የተነሱ መሪዎች አሏት፤ አፍሪካ በትክክለኛው መንገድ እየተጓዘችም ነው” ሲሉ አክለዋል።
“ኢትዮጵያና ጋምቢያ ያላቸው ግንኙነት በጣም ጥሩ የሚባል ነው” ያሉት ሚኒስትሩ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ከዚህ ቀደም መፈራረማቸውን አስታውሰዋል።