ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት 6 ወራት ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

ጥር 4/2015 (ዋልታ) ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት 70 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት በአጠቃይ ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

ተቋሙ የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፓርት ለባለድርሻ አካላትና ለሚዲያ ባለሙያዎች እያቀረበ ይገኛል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት 70 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት 33 ነጥብ 8 ቢሊየን አጠቃላይ ገቢ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 8 ነጥብ 18 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን ተቋሙ አስታውቋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተቋማችን የአገልግሎት ጥራትን በማሳደግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና ደንበኞች በአገልግሎት አሰጣጥ እንዲረኩ ለማድረግ ሰርተናል፤ ውጤታማም ሆነናል ብለዋል።

ተቋሙ ከመደበኛ አገልግሎት አሰጣጥ ባሻገር የተጀመረው የቴሌ ብር አገልግሎት፤ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት በተጨማሪም የፋይናንስ አካታችነት ለማረጋገጥና ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልፀዋል፡፡

ከቴሌ ብር 27 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደንበኞች ማፍራት መቻሉንና 166 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የግብይት መጠን በማንቀሳቀስ 82 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ ማስገኘት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪ 18 ባንኮችን ጨምሮ በርካታ የግልና የመንግስት ተቋማት ከቴሌ ብር ጋር በጋራ መስራት ላይ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በተለይም ወጪን በአግባብ በመጠቀም ረገድ ትልቅ ስራ መሰራቱን ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ከዚህም 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ ቅነሳ መደረጉን ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም መሪ የተሰኘ የሶስት አመት የእድገት ስትራቴጂ ቀርፆ ወደ ስራ የገባ መሆኑን ሀምሌ 1 ቀን 2014 ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

በሳራ ስዩም