ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌ ብር-ኢንጌጅ” የተባለ አዲስ አገልግሎት አስጀመረ

ሚያዚያ 7/2016(አዲታ ዋልታ) ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌ ብር-ኢንጌጅ” የተሰኘ አዲስ አግለግሎት መስጠት መጀመሩን ይፋ አደረገ።

አገልግሎቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንደገለጹት፣ኩባንያው በሁሉም ዘርፍ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ ያለ ኢንተርኔት ክፍያ በደንበኞች መካከል መረጃዎችን መለዋወጥ ፣ ገንዘብ ማስተላለፍ፣ ክፍያዎችን መፈጸም እና መሰል አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።

አገልግሎቱ በዲጂታል ፋይናንስ ሽግግር ውስጥ የንግድ፣ የመንግስትና የግል ተቋማትን ትኩረት በማድረግ የዲጂታል ኢኮኖሚ ምህዳሩን ለማስፋት የሚረዳ ነው ብለዋል።

የግለሰብም ሆነ የንግድ ደንበኞች የተናጠል ወይም የቡድን ቀጥታ ውይይቶችን ለማድረግ፣ የግብይት መረጃዎችን ለመለዋወጥ፣ በውይይቶች ወቅት ገንዘብ ለመላክና ለመቀበል እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በአዲሱ አገልግሎት ደንበኞች የንግድ ወይም ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን በፅሁፍ፣ በፎቶ፣ በድምጽ፣ በቪዲዮና በሰነድ መልክ መለዋወጥ እንደሚያስችላቸው ኢትዮ ቴሌኮም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።