ኢንስቲትዩቱ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባው የእንስሳት መድኃኒት ፋብሪካ ተመረቀ

ሚያዝያ 16/2013 (ዋልታ) – ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ያስገነባው የእንስሳት መድኃኒት ፋብሪካ ተመረቀ።

ኢንስቲትዩቱ በቢሾፍቱ ከተማ ያስመረቀው የመድኃኒት ፋብሪካ ለግንባታና ለመሳሪያ ተከላ ከ100 ሚሊዮን በላይ ብር ወጭ ተደርጎበታል።

የፋብሪካው ወደ ስራ መግባት አገሪቱ ለእንስሳት መድኀኒት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይቀንሳል ተብሏል ።

የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማርታ ያሚን በምርቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ክትባቶችን በማምረትና በማሰራጨት በተለይም ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል።

ለተለያዩ አገራት የእንስሳት ክትባቶችን በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑንም ገልጸው፤ ኢንስቲትዩቱ ክትባቶችን በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ባለፈ በክትባት ዙሪያ ምርምርና ጥናቶችን እየሰራ መሆኑን ዶክተር ማርታ አብራርተዋል።

በዛሬው እለት ያስመረቀው ፋብሪካም የግብርናውን ዘርፍ ከመደገፍ በተጨማሪ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ደርሻ እንደሚኖረው ለኢዜአ ተናግረዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ቢሾፍቱ የሚገኘው ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በ1956 ዓ.ም የተመሰረተ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።