የፌዴራሊዝም ስርአቱ የአተገባበር ችግር በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ላይ እንከን ፈጥሯል – ሰላም ሚኒስቴር

ሚያዝያ 16/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ የነበረው የፌዴራሊዝም ስርዓት የአተገባበር ችግር በአገሪቷ ትክክለኛ የዴሞክራሲ ስርአት እንዳይገነባ እንከን ሆኖ መቆየቱን ሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።

ሰላም ሚኒስቴር ያዘጋጀው የፌዴራሊዝምና የሰላም ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት በአዳማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ፌዴራዝምና ለፌዴራሊዝም የስኬት ቁልፎች፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የቋንቋ ብዝሃነት በአለም አቀፋዊው ዕይታ፣ ፌዴራሊዝምና የውድድርና የትብብር ሥርዓቶች እና የግጭት አፈታት ሥራዓትን የሚዳስስ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ይደረጋል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፈን ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት መከተል ከጀመረች ሶስት አስርት አመታት ብታስቆጥርም በትግበራ እና አፈፃፀም ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት እየተገነባ እንዳይሄድ እና በህገ- መንግስቱ የተደነገጉ መብቶች በአግባቡ ተፈፃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በዚህም ከህዝቡ የሚነሱ አዳዲስና ወቅታዊ ጥያቄዎችን በተገቢ መንገድ ለመመለስ የሚያስችል ብቃት እንዳይኖር አድርጓል ነው ያሉት።

በርካታው ህዝብም በፌዴራሊዝም ላይ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር በስርዓቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ማድረጉንም ዶክተር ስዩም ገልፀዋል።

የሰላም ሚኒስቴር በነዚህ በተከባለሉ ችግሮች ምክንያት ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመፍታትና ብዥታዎችን ለማጥራት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬው የውይይት መድረክም የዚሁ አንድ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት በጥናት ላይ የተመሰረተ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት የሚካሄድበት መሆኑን አስረድተዋል።

ሚኒስቴሩ መድረኮችን በአውደ ጥናት፣ ኮንፈረንስ፣ ፓናሎችና ፎረሞችን በማዘጋጅት ተከታታይ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በመድረኩ በርካታ ምሁራን የተሳተፉበት ሲሆን “ፌዴራሊዝምና የሰላም ግንባታ በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናጣይ እንደሚካሄድ የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።