ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮው ከባለሀብቶች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው

ነሀሴ 17/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በከተማዋ ካሉ ባለሀብቶች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡

ከለውጡ በፊት በንግድ ዘርፍ ከፍተኛ ተግዳሮቶች የነበሩ ሲሆን በተለይም የመንግሥት ደጋፊ የሆነ ነጋዴዎች ልማታዊ፤ ደጋፊ ያልሆነ ደግሞ አፍራሽ እየተባሉ የሚፈረጁበት ስርዓት እንደነበር በመድረኩ ተነስቷል፡፡

አሁን ላይ በተለይም ከለውጡ ወዲህ የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ እና ለማሻሻል በርካታ ስራዎች መሰራታቸው የተነሳ ሲሆን ለአብነትም ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው  አሳሪ የንግድ ህግ በመሻር አዲስ እና ዘመኑን የዋጀ የንግድ ህግ እንዲፀድቅ መደረጉ አንዱ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

የግሉ ዘርፍ በተለይም ባለሀብቱ መንግሥት በፈጠረለት እድል በመጠቀም መንግሥት ለሚያደርገው ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ሲሰራ የቆየ ሲሆን ለአብነትም  ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፣ ለአረንጓዴ አሻራ ፣ ለገበታ ለሀገር፣ ለመከላከያ ሰራዊት እና ለሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም አሁን ላይም ሀገር የህልውና ዘመቻ ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት የግሉ ዘርፍ እና ባለሀብት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት ከማቅረብ ጀምሮ ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ነው የተገለፀው።

የንግድ ተዋንያንም ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ሀገራዊ ሀላፊነታችንን እንወጣለን ያሉ ሲሆን መንግስትም ያለብንን የግብዓት እጥረት ተመልክቶ እገዛ ያድርግልን  ብለዋል፡፡

እየተከሰተ ያለውን የኢኮኖሚ አሻጥር ለመቆጣጠር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑም ታውቋል፡፡

ግብረ ሀይሉ የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈጥሩ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋልም  ተብሏል፡፡

(በሜሮን መስፍን)