ኢትዮጵያ ከቻይና መንግስት የተላከላትን 300 ሺህ ዶዝ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ተረከበች

ኢትዮጵያ ከቻይና መንግስት የተላከላትን 300 ሺህ ዶዝ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ተረከበችነሐሴ 17/2013 (ዋልታ) –ኢትዮጵያ ከቻይና መንግስት የተላከላትን 300 ሺህ ዶዝ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተረክበዋል።

ክትባቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዥያዎ ዢዮዋን ለዶክተር ሊያ ታደሰ አስረክበዋል።

አምባሳደሩ ዢዮዋን ቻይና ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት በምታደርገው ጥረት አጋር መሆኗን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ቤጂንግ በኮቫክስ ጥምረት በኩል 300 ሺህ ዶዝ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት መላኳንም ጨምረው ገልፀዋል።

የቻይና መንግስት ላደረገው ድጋፍ ያመሰገኑት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ክትባቱ ተጠናክሮ ለቀጠለው የመከላከል ጥረት አጋዥ ይሆናል ብለዋል።

ክትባቱ በዋናነት በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደውልም ተነግሯል።

ቻይና በዛሬው ዕለት የላከችውን 300 ሺህ ዶዝ ክትባትን ጨምሮ እስካሁን ባለው ሂደት ለኢትዮጵያ 1 ሚሊየን ዶዝ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ድጋፍ አድርጋለች ሲል ኤኤምኤን ዘግቧል።