ባንኩ ባለፉት 6 ወራት በዲጂታል ባንክ አማራጮች 1.3 ትሪሊዮን ብር ዝውውር ማድረጉን አስታወቀ

ጥር 24/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት የዲጂታል ባንክ አማራጮች በመጠቀም 1.3 ትሪሊዮን ብር ዝውውር ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የባንኩ የ2015 ግማሽ በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀሙን የገመገመበትን ጉባኤ የባንኩ ማኔጅመንት አባላት እና የየዲስትሪክቶች ኃላፊዎች በተገኙበት አከናውኗል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ በበርካታ ዘርፎች ስኬታማ አፈፃፀም አስመዝግቧል፤ ከነዚህም መካከል የዲጂታል ባንክ አገልግሎቱ ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡

በውጤቱም በርካታ ደንበኞች ገንዘባቸውን ለማስተላለፍ የዲጂታል ባንኪንግ አማራጮችን ተመራጭ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡

የተገኙ መልካም ውጤቶችን በማስጠበቅ በበጀት ዓመቱ የተያዙ እቅዶችን ከልዩ ልዩ መመዘኛዎች አንፃር ስኬታማ ሆኖ ለማጠናቀቅ ሁሉም የባንኩ ሰራተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ ፕሬዝዳንቱ ማሳሰባቸውን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡