እስራኤል ኢትዮጵያን አስፈላጊ በሆነ መንገድ እንደሚትደግፍ ገለጸች

ጥር 17/2014 (ዋልታ) በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ ከእስራኤል ፕሬዝዳንት የውጭ ፖሊሲ አማካሪ ከሆኑት አምባሳደር ዚቪ ቪፒኒ ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በሁለትዮሽ ግኑኝነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይቱ አምባሳደር ረታ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም አሸባሪው ሕወሓት በአፋርና አማራ ክልሎች የፈጸመውን ግፍና በደል አስረድተዋል።
 
አሁን ላይ መንግሥት ለፖለቲካዊ መፍትሄ እና ለሰላም በሩን ክፍት በማድረግ፣ ሁሉን ዐቀፍ የውይይት መድረክ ለመጀመር ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
 
ውይይቱ ሁሉን አካታች እንዲሆን ለማድረግና አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን፣ ለዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን አገራዊ ምክክር አዋጅ ማፅደቁን፣ የሚቋቋመው ኮሚሽን ለውይይት አጀንዳ የሆኑ ጉዳዮችን ለማቅረብ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
በዚህም ውይይት የሚሳተፉት የፖለቲካ ድርጅቶች ለሰላማዊ ትግል የተዘጋጁ የኃይል አማራጭን የማይከተሉት መሆን እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።
 
አምባሳደር ዚቪ በበኩላቸው እስራኤል እንደወዳጅ አገር የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት እንደምትፈልግ እና የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም እንደሚረዱ ገልፀው የኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሄደበት መንገድ የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
 
የእስራኤል መንግስትም ኢትዮጵያን አስፈላጊ በሆነ መንገድ እንደሚደግፍ ማስታወቃቸውን ከእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
 
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://www.facebook.com/waltainfo
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!