አሸባሪው ሸኔ 325 ሺሕ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ ማድረጉ ተገለፀ

ጥር 17/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሸኔ በኦሮሚያ ክልል በትምህርት ተቋማት ላይ ባደረሰው ውድመት 325 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መናጠባቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ባለፈው አንድ ዓመት በትምህርት ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን እና ያጋጠሙ ችግሮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኃላፊው በመግለጫቸው በአሸባሪው ሸኔ የጥፋት ተግባር ከ163 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን፣ 756 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ሃብትና ንብረታቸው መዘረፉን ተናግረዋል።

በዚህም 325 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸው ነው ያሳወቁት፡፡ በተጨማሪም በሽብር ቡድኑ ተግባር ከ5 ሺሕ በላይ መምህራን ሙሉ በሙሉ ከሥራ ገበታቸው ውጭ ስለመሆናቸው መግለጻቸውን ነው ኢቢሲ የዘገበው፡፡