ከተሞቻችን-አዲግራት



በ14ኛው ክፍለ ዘመን እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ታሪካዊቷ የአዲግራት ከተማ ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ 1ሺሕ 38 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

የአመለሸጋ ሕዝብ መገኛ፣ የአብሮነት ማሳያና በእንግዳ አክባሪነቷ ተምሳሌት የሆነች ከተማ ናት፡፡

ከተማዋ ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 457 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን ደጋማ የአየር ፀባይ አላት፡፡

ለከተማዋ ስያሜ የሆነውና “አዲግራት” የሚለው ቃል ትግርኛ ሲሆን ትርጓሜውም “የእርሻ መሬት ሀገር” እንደ ማለት ነው።

በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተገነባ የሚነገርለት “ደብረ ዳሞ” እና የ”ጉንዳ ጉንዶ” ገዳማት በአዲግራት አካባቢ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው፡፡

የከተማዋ ተወላጆች ከየአሉበት ተሰባስበው ከወላጆቻቸው ጋር የመስቀል እና የአረፋ በዓላትን በድምቀት የሚያከበሩባት ከተማ ነች።

አብዛኞቹ የአዲግራት ከተማ ተወላጆች ዋነኛ የስራ መለያቸው ንግድ ነው።

አዲግራት የተለያዩ የሰፈር ስያሜዎች ያሏት ሲሆን ሜዳ አጋመ፣ ፒያሳ፣ ዜሮ ሶስት፣ ጎልጎልታ፤ ሐድሽ አዲ እና መነሀሪያ ተጠቃሽ ናቸው።

አዲግራት “ጥህሎ” በሚባል ተወዳጅ ባህላዊ ምግብ የምትታወቅ ሲሆን ከንፁህ ማር በሚዘጋጅ ንፁህ ጠጅም ትታወቃለች።

ፍሉይ፣ ሜዳ አጋመ እና ውልዋሎ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ አጋዚ ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም ሁለት የግል ኮሌጆች እና የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ በከተማዋ ይገኛሉ።

በሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ አጋሞስ፣ ካነን ኢንተርናሽናል፣ ሰቲት ሁመራ እና ሆሆማ ሆቴሎች ይገኛሉ።

አዲግራት ለሀገር ባለውለታ የሆኑ ብዙ ታዋቂ ሰዎችን ያፈራች ሲሆን ከእነዚህም መካከል ድምፃዊ ባህታ ገ/ህይወት፣ ደራሲ ካሳሁን ገ/ጊዮርግስ እንዲሁም የኦሎምፒክ ጀግናው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ከዚያው አካባቢ የተገኙ ናቸው፡፡

አዲግራት ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁም ሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትዝታችሁን አጋሩን። መልካም ሳምንት!!

በአዲስዓለም ግደይ