እንሰት ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችበት ትልቅ ሃብት መሆኑ ተገለጸ

እንሰት ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችበት ትልቅ ሀብት መሆኑን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮቴክኖሎጂ መምህር እና ተመራማሪ ዶክተር አዲሱ ፍቃዱ ገለጹ።

ዶክተር አዲሱ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ እንሰት 20 ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሦስት ጊዜ መመገብ የሚያስችል እንደ ሀገር ያልተጠቀምንበት ሲሳይ፤ እስካሁን በጣም ያጣነው ትልቅ ሀብት ነው።

ህዝቡ በባህላዊ መንገድ ለራሱ ምግብ አዘጋጅቶ ከመጠቀም ውጪ ለገበያ በማቅረብ ገቢ ማግኘት ባለመቻሉ እንደሀገር ትልቅ የሀብት ብክነት አለ ያሉት ተመራማሪው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ እያንዳንዱ ከመቶ በላይ እንሰት ቢኖረውም ለምግብ የሚያውለው ግን ከአምስት አይበልጥም ብለዋል። ነገር ግን ቀሪውን በዘመናዊ መንገድ አምርቶ ለገበያ የሚቀርብበት መንገድ ቢኖር ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ገበያ መቅረብ የሚችል እምቅ ሀብት እንደሆነ ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ ከእንሰት ማግኘት የሚገባን ጥቅም ሩቡንም ማግኘት አልተቻለም ያሉት ተመራማሪው፣ በባህላዊ መንገድ የሚፋቅበት ዘዴ እና የሚጓጓዝበት መንገድ ኋላቀር በመሆኑ ከአንድ እንሰት ከ24 እስከ 25 በመቶ የሚሆነው ይበላሻል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተለይም ከፍተኛ የሆነ የእንሰት ክምችት በሚገኝባቸው የሲዳማ፣ ደቡብ እና አንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች በመዘዋወር ባካሔደው ጥናት እንሰት በባህላዊ መንገድ በሚዘጋጅበት ወቅት ከፍተኛ በሆነ ደረጃ እንደሚባክን ማረጋገጥ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

እንደ ዶከተር ፍቃዱ ገለፃ ፣ እንሰትን በትክክል እና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ቢደረግ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ቢሆንም በትክክል ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ትኩረት አልተሰጠውም።

ዩኒቨርሲቲው እንሰት ላይ ከ5 ዓመት በላይ ጥናት እና ምርምር በማድረግ በብዙ መልኩ በማዘጋጀት ለምግብ አገልግሎት መዋል የሚችል መሆኑን በጥናት ግኝታቸው ያረጋገጡ መሆኑን ጠቁመዋል። ድርቅ መቋቋም አቅሙም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

እንሰት ትኩረት ቢሰጠው ከጤፍ እኩል የሚሆንበት አጋጣሚ እንዳለ የገለጹት ተመራማሪው፣ የምግብ ዋስትናን እንደሀገር ለማረጋገጥ ወሳኝ ምርት ነው ብለዋል። ጉዳዩ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት የተነፈገው በመሆኑ አርሶ አደሩ እንሰቱን እየነቀለ ወደ ጫት ማሳውን እያዞረ እንደሆነ አመልክተዋል።

ይህን ስጋት ለመቀነስ ዩኒቨርሲቲው እንሰት  ሳይባክን እየተዘጋጀ ለምግብነት የሚውልበትን መንገድ የማብላያ ማሰሮ እና እርሾ በማዘጋጀት ምርታማ መሆን እንደሚቻል ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ፣ የምርምር ውጤቱ ህዝቡ ጋር እንዲደርስ የባለድርሻ አካላትን ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።