የጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በድጋሚ መባባሱንና መዛመቱን ተከትሎ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር “እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ” የሚል ንቅናቄ በአዲስ መልክ በይፋ አስጀምሯል።
በማስጀመሪያ መድረክ ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በቫይረሱ ሳቢያ ለሞቱ ዜጎች የህሊና ፀሎት የተደረገበ ሲሆን፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት አመራሮች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ባስተላለፉት መልዕክት ህብረተሰቡ ገዳይ ከሆነው የኮሮና ቫይረስ ራሱን በመጠበቅ ከሚስተዋለው ቸልተኝነትና መዘናጋት ወጥተው የጤና ባለሙያዎችን ምክርና የንቅናቄ ደጋፊ መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር ዓባይ በበኩላቸው፣ በሁሉም እርከን ያለን አመራሮች ለዜጎቻችን አርአያ በመሆን ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ዛሬ የተጀመረው ንቅናቄ የሁሉም ማህበራዊ እና ግላዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ አቅማችንን ያበረታል፤ የበሽታውን ሥርጭትም ይገታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወክለው የተገኙት መጋቢ ታምራት አበጋዝ በበኩላቸው፣ “መንፈሳዊ ስርአቶቻችንን ርቀታችንን ጠብቀን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መተግበራችንን ሳንዘነጋ ይህንን ወረርሽኝ ልንከላከል ይገባል” ብለዋል፡፡
ዛሬ ይፋ ለተደረገው የ“እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ” ንቅናቄም ህብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን፣ ከ2ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
መድረኩን የጤና ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጋራ እንዳዘጋጁት ታውቋል፡