እንግሊዝ ሩስያን ጦርነት ከገጠመች የጦር መሣሪያ ትጨርሳለች ሲል አንድ ቡድን አስጠነቀቀ

እንግሊዝ በምዕራብ አውሮጳ ከሩስያ ጋር የምትላተም ከሆነ የብሪታኒያ እግረኛ ወታደሮች ከጦር መሣሪያ ውጭ ይሆናሉ ይላል አንድ ቡድን።

ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስስ የተሰኘው ተቋም ምንም እንኳ የብሪታኒያ ጦር የሰሜን አትላንቲክ ጦር የቃል-ኪዳን ድርጅት [ኔቶ] አባል ቢሆንም አሳሳቢ የጦር መሣሪያና ቀለሃ እጥረት አለበት።

የዩናይትድ ኪንግደም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት በበኩሉ፤ ሃገራቸው ከኔቶ ጋር እየሠራች እንዳለችና በቂ የሆነ የጦር መሣሪያ እንዳላት ተናግረዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት የኔቶን 70ኛ ዓመት ለመዘከር አባላቱ ሎንዶን ከተማ ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸውን ተከትሎ ነው ጥናቱ የደረሰበትን ይፋ ያደረገው።

እንግሊዝና ሌሎች የኔቶ አባላት ሩስያ በምዕራብ ሩስያ በኩል አደጋ እንዳትደቅን በማለት ጦረኞቻቸውን በተጠንቀቅ አቁመዋል።

በኢስቶኒያ ግዛት ከሚገኙት ወታደሮች መካከል ከሁለት ዓመት በፊት ወደሥፍራው ያቀኑ 800 የእንግሊዝ ወታደሮች አሉ።

በሥፍራው የቆመውን ወታደር የጦር መሣሪያ አቅም ከሩስያ ያነፃፀረው ይህ ጥናት ሃገሪቱ የሩስያ ጦር የመቋቋም አቅም የላትም ሲል ደምድሟል።

የሩስያ ጦር ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን ለመገመት በግሪጎሪ አቆጣጠር 2014 ላይ ሁለት የዩክሬን ባታሊዮኖችን በደቂቃዎች እንዴት እንደደመሰሰ ማሰብ ብቻ በቂ ነው ባይ ጥናቱ።

ጥናቱ እንደ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ የሚያየው የጦር መሣሪያ እጥረትን ብቻ ሳይሆን የቀለሃንም ጭምር ነው።

ለጥናቱ ምላሽ የሰጠው የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት እንግሊዝ ሩስያን ለመመከት ከአጋሮች ጋር እንጂ ብቻዋን አትደክምም ሲል ተደምጧል።

ከሶስት ሳምንታት በፊት የረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማኽሮን ኔቶ ‘አእምሮው የበሰበሰ’ ሲሉ ቃል-ኪዳኑን ወርፈዋል።

የእንግሊዝ ፖለቲከኞች መከላከያ ሠራዊቱ የበጀት ቀዳዳ አለበት ሲሉ ይወቅሳሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉዊቴሬዝ ‘ቀዝቃዛው ጦርነት’ ተመልሶ እየመጣ ነው በሃገራት መካከል ያለው ውጥረት ሊረግብ ይገባል ይላሉ።

ምንጭ ፦ ቢቢሲ