እየተሻሻለ ባለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ ስልጠና  እየተሰጠ ነው

ጥቅምት 4/2014 (ዋልታ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሀገራዊ እና ተቋማዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ለአምባሳደሮች፣ ለዲኘሎማቶ፤ ለኢምግሬሽን እና ሌሎች ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
በዛሬው እለትም እየተሻሻለ ባለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል።
በዚህም እየተሻሻለ ያለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከቀድሞው ፖሊሲ በተለየ ሁኔታ የጠፈር ሳይንስ፣ ፍልሰት፣ የሳይበር፣ የባህር ኃይል እንዲሁም ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ያካተተ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ብርቱካን አክለውም ረቂቅ የፖሊሲ ሰነዱ በተለያዩ መድረኮች ብዙ ውይይት ተደርጎ ግብዓቶች በመውሰድ የመጨረሻ ቅርፅ እንዲይዝ መደረጉን ጠቅሰው፣ በቅርቡም ፀድቆ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል።
ስለጠናውን የሰጡት የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ካሳሁን ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) እንዳሉት ፖሊሲውን ማሻሻል ያስፈለገው ነባሩ ፖሊሲ ከተረቀቀበት ጊዜ ወዲህ አገራዊ ፣ ክልላዊ እና አለምአቀፋዊ ሁኔታዎች በብዙ መልኩ በመቀየራቸው ነው።
እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ ተራማጅ ፖሊሲ መተግበር በማስፈለጉ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
አዲሱ ፖሊሲ ለውስጣዊ ሁኔታዎች ትኩረት እንደሚሰጥ የተገለፀ ሲሆን፣ ሀገራዊ የለውጥ እሳቤዎችን፣ የውጭ ግንኙነት መርሆዎችን እንዲሁም አለምአቀፍ ህጎችን ማዕከል ማድረጉን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡