ከሰል በችርቻሮ እየሸጡ የ600 ሺሕ ብር ቦንድ የገዙ እናት

አሰለፈች ፀጋዬ ይባላሉ። የሻሸመኔ ነዋሪ ናቸው። ጉሊት እየቸረቸሩ ከሚያገኟት ገንዘብ በመቆጠብ ከ600 ሺሕ ብር በላይ ቦንድ ገዝተዋል፡፡ የኢትየጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ጊዜ ጀምሮ ከሰል እየሸጡ ከሚያገኟት ፍራንክ ቀንሰው ለ13 ዓመታት ያለማቋረጥ ቦንድ የገዙ ሀገር ወዳድ እናት ናቸው። ለሀገር ፍቅር የሚከፈል ትልቅ ዋጋ ማለት ለመስጠት ብዙ በረከቶችን መፈለግ ሳይሆን ያለን አንጠፍጥፎ ለነገዋ ኢትዮጵያ ብርሃን ከመቀነት አውጥቶ መስጠት ስለመሆኑ እኚህ እናት ምሳሌ ናቸው።

ቦንድ የምገዛው በ2003 ዓ.ም መጋቢት 24 መሰረተ ድንጋዩ በያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከተቀመጠ ጀምሮ ነው የሚሉት አሰለፈች ከዚያ ቀን ጀምሮ እስካሁን አቋርጠው እንደማያውቁ ይናገራሉ።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሕይወታችን፣ ደማችን፣ ስጋችን እና ቅርሳችን ስለሆነ እኔ አሻራየን አሳርፌ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ስራ ሰርቼ ማለፍ እፈልጋለሁ ይላሉ።

በእድሜ አመሻሽ የሚመጣን የማን ይጦረኛል ፍራቻ፣ ስሞትስ እንዴት እቀበራለሁ የሚል ጥያቄ ሳያሳስባቸው ያሳለፉት የጨለማ ኑሮ እንዲሁም በእንጨት እያበሰሉ መኖርን ቀጣዩ ትውልድ እንዳያየው በማሰብ ቦንድ በመግዛት የሕዳሴ ግድብ ከዳር እንዲደርስ የራሳቸውን ሚና የተወጡ፤ እየተወጡም የሚገኙ እናት ናቸው።

ቅመማ ቅመምን ጨምሮ ከሰል፣ ሽሮ እና በርበሬ ጉሊት ላይ በመቸርቸር የሚተዳደሩት እናት ካለቻቸው ላይ ቆጥበው ለሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ገንዘባቸውን ብቻ በመለገስ አያበቁም።

ከዚያም በላይ ግድቡ እንዳይጠናቀቅ የሚጥሩ የውጭ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማሳሰብን ይጨምራል። “በእኛ ውሃ የሚጠቀሙ ኃይሎች መልሰው ለእኛ ሩዝ ይልኩልናል፤ እና በራሳችን ውሃ ሌሎችን ሳንጎዳ መጠቀም መብታችን ነው” ይላሉ።

መላው ኢትዮጵያዊያን በቻሉት አቅም ሀገራቸውን ለማልማት ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን ያቀርባሉ።