ለኮሪደር ልማት የሚፈርሱ ሕንፃዎች ከቢሮውና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት በማድረግ የተከናወነ ነው – ባለስልጣኑ

የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው

መጋቢት 25/2016 (አዲስ ዋልታ) የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የሚፈርሱ ሕንፃዎች መስፈርት የወጣላቸውና በመስፈርቱ መሰረት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመሆን ውይይት ተደርጎባቸው የተከናወኑ መሆናቸውን አስታወቀ።

የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው በአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ላይ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ሁኔታ ምን ይመስላል በሚለው ጉዳይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ባለስልጣኑ የከተማ ስነ-ሕንፃ ቅርስን በተመለከተ ከሶስት ሀገራት በወሰደው ተሞክሮ መሰረት መስፈርቶችን በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱን ገልፀዋል።

በዚህ መሰረት ስነ-ሕንፃው፣ ዘይቤ /style/፣ አገነባቡ፣ እድሜው እንዲሁም ውጫዊና ውስጣዊ ንድፉ፣ ከግለሰብ፣ ከሁነትና ከዳራ ጋር የተያያዘ ታሪክ፣ ከባቢው፣ መልከዓ ምድሩና አገልግሎቱ፣ የቅርስ ሁኔታው ተጠብቋል ወይ በሚል መስፈርት ከመቶ ተመዝኗል።

በዚህ መስፈርት መሰረት ከ64 በመቶ በላይ ያመጡ የማይነኩ ቅርሶች፣ ከ50 እስከ 64 በመቶ ያገኙት እንደሁኔታው ማሻሻያ የሚደረግባቸው ሲሆን ከ50 በታች ያሉት ደግሞ የቅርስነት መስፈርትን ያላሟሉ ሆነዋል ተብሏል።

አብዛኞቹ ቅርሶች በየዘመኑ የተደረገባቸው ለውጥ የቅርስነት መስፈርት እንዳያሟሉ እንዳደረጋቸውም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

አጨቃጫቂ ህንፃዎች ላይ የባለሙያዎች ምዘና እየተካሄደ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና ልማትን አስማምቶ ለመቀጠል እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

በብሩክታዊት አፈሩ