ከሴኔጋላዊው ዓለም አቀፍ አርቲስት ጋር በፋሽን ዲዛይንና ግራፊክስ አርት ጥበብ ዙሪያ ውይይት ተደረገ

ሚያዚያ 7/2013(ዋልታ) – የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ፋሽን ዲዛይነሮች ማህበር ጋር በመሆን ከሴኔጋላዊ የፋሽንና ግራፊክስ ዲዛይነር አል ሓጂ ባባካር ሲላ ጋር በኢትዮጵያ የባህል ኢንዱስትሪ ዙሪያ እና ቀጣይ አብሮ መሥራት ስለሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንድስትሪ ልማት ዳይሬክቶሬት እና የኢትዮጵያ ፋሽን ዲዛይነሮች ማህበር አመራሮች እና አባላት ተሳትፈዋል።

ሓጂ ባባካር ሲላ በሴኔጋል አገር አቀፍ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ማዕከል የዲዛይን እና ግራፊክስ ስነ ጥበብ አሰልጣኝ ኮሚኒኬተር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ዲዮግ አፕ የተባለ ፕሮጀክት በመቅረጽ ከሴኔጋል ባህልና ኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር እና ንግድና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጋራ እየሠራ ይገኛል፡፡

ይህንኑ ፕሮጀክት ለማስተዋወቅና በኢትዮጵያ ከሚገኙ የዘርፉ ሙያተኞች ጋር በጋራ ለመሥራት እንዲቻል ከዘርፉ ማህበራት ጋር በመወያየትና የመስክ ጉብኝት እያደረገ ነው ተብሏል።

አርቲስቱ የቆዳ አልባሳት፣ ጫማ ዲዛይንና ፋሽን ድርጅት ባለቤት ሲሆን ቀደም ብሎም በተለያዩ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት ሙያውን በማስተዋወቅ ቆይቷል።

ይህንኑ የስራ ፈጠራ፣ ፋሽንና ግራፊክሰ አርት ከኢትዮጵያ ሙያተኞች ጋር ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሷል።

ይህ ሴኔጋላዊ አርቲስት በአሁኑ ጊዜም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የክብር አምባሳደር ሆኖ አየር መንገዱን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኝ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡