ከሽግግር ፍትሕ ምን ይጠበቃል?

በብርሃኑ አበራ

በሰሜኑ ኢትዮጵያ የተካሄደውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት በፌደራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል በፕሪቶሪያ ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል፡፡ በዚህም መንግሥት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ከዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል፡፡

በዚህም መሰረተ ልማቶችን መልሶ ከመጠገን እና ከማስጀመር ባሻገር በሕዝቦች መካከል መተማመን እና ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ሁሉንም የሚያሳትፍ፣ የሕግ ተጠያቂነት፣ ፍትሕ፣ እርቅና ካሳን ጭምር ታሳቢ የሚያደርግ ብሔራዊ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ለመተግበር ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡

በግጭቱ ውስጥ ባለፈች አንድ ሀገር የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለማጥራት እና እርቅ ለመፍጠር የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ መሆኑ የሚጠቀስ ሲሆን ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡

የሽግግር ፍትህ ለተጎጂዎች እውቅና ለመስጠት፣ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የግለሰቦችን አመኔታ ለማሳደግ፣ የሰብዓዊ መብት መከበርን ለማረጋገጥ እና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እንዲሁም በሕዝቦች መካከል እርቅ ለመፍጠር አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡

ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት፣ በሕዝቦች መካከል መተማመንን ለመፍጠር፣ በጦርነቱ ለተከሰቱ የመብት ጥሰቶች እና ወንጀሎች ምላሽ በመስጠት ረገድ እንዲሁም ከልዩነት ትርክቶች እና ቁርሾዎች ለመውጣት ፍትሕን ማስፈን እና እርቅን ማምጣት አስፈላጊ በመሆኑ የሽግግር ፍትሕን እውን ለማድረግ አማራጭ ፖሊሲ አፈላላጊ ቡድን ተዋቅሮ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ሒደቱ የኢትዮጵያዊያንን ፍላጎት ያማከለና በራሳቸው ተነሳሽነት የሚተገበር ሲሆን ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎችን መመልከት ለስኬታማነቱ ወሳኝ በመሆኑ በሽግግር ፍትህ ላይ ልምድ ያካበቱ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት እና ባለሙያዎችን ተሞክሮ በማጤንም ጭምር ቡድኑ አማራጭ እያፈላለገ ይገኛል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ጥልቅ እውነቶችን ለማግኘት በተለይም ጭፍን ጥላቻን የሚያስከትሉ ትርክቶችን ፈትሾ እና አንጥሮ ለማውጣት የሚደረግ ሒደት ሲሆን ለዘላቂ ሰላም እርቅን መፍጠር ላይ ያለመ ነው፡፡

የሽግግር ጊዜ ሒደት የወንጀል ክስ ላይ የሚያተኩር፣ አጥፊዎችን በወንጀል የሚጠይቅ፣ ይቅርታ የሚወርድበት ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት ክስ ሳይመሠረት ጥፋቱ እንዲታወቅ፤ አጥፊዎች ይቅርታ እንዲጠይቁ እና ተበዳዮችም ይቅርታውን እንዲቀበሉ የሚደረግበት የፍትሕ ሒደት ነው፡፡

የተለያዩ ሀገራት የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ አድርገው እውነትን አፈላልገው፣ የተጎዱ ሰዎችን ክሰው፣ ለወንጀለኞች ፍርድ ሰጥተው እንደ ሀገር ቀጥለዋል፡፡

ለዚህም እንደ ምሳሌ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋምቢያ፣ ሩዋንዳ፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቺሊ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ሀገራትን ተሞክሮ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ደቡብ አፍሪካ

ደቡብ አፍሪካ የእውነት እና የእርቅ ኮሚሽን አዋቅራ በአፓርታይድ ሥርዓት በሀገሪቱ የተፈጠሩ የጥቃት፣ የጥላቻ እና የመድልኦ ታሪክ እንድታስወግድ ያስቻላትን ሒደት እንመልከት፡፡

እ.ኤ.አ. በ1994 ደቡብ አፍሪካ ለ50 ዓመታት የዘለቀ የአፓርታይድ የጭቆና ስርዓት ዘመን አብቅቶ ሀገሪቱ ነጻነቷን ስታውጅ በጨቋኝ ስርዓቱ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማስተካከል እንዲሁም ተጠቂዎች እና ወንጀለኞችንም ለይቶ ፍርድ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ የሽግግር ፍትሕ (የእውነት እና እርቅ ኮሚሽን) በመተግበር የሚተማመን እና እርቅ የሰፈነበት ማህበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ነበር፡፡

ኮሚሽኑ በአፓርታይድ ወቅት የተፈፀሙ ወንጀሎችን በማጥራት ፍትህ እና እርቅን በማምጣት ረገድ በሰራው ውጤታማ ሥራ በሕዝቦች መካከል መተማመንን እና ሰላምን መፍጠር የቻለ ሲሆን የሀገሪቱን የቀጣይ ጉዞ ለመቀየስ መሠረት የጣለ መሆኑም ይነገርለታል፡፡

ሩዋንዳ

በሩዋንዳ በጥላቻ ንግግር ውጤት በፈረንጆቹ 1994 በቱትሲዎች ላይ በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ከ800 ሺሕ እስከ 1 ሚሊየን የሚሆኑ ቱትሲዎች በወንድም ዜጎቻቸው በሁቱዎች እጅ እንደቅጠል ረግፈዋል፡፡

ሩዋንዳ ከዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በኋላ ሀገር በቀል የዳኝነት ስርዓት በማቋቋም ወደ እርቅና ሀገር ግንባታ በመግባት ተበዳዮች ተክሰው፤ በዳዮች ለፍርድ ቀርበው የዘር ፍጅቱ በሽግግር ወቅት ፍትህ ተቋጭቷል፡፡ ሒደቱም ለሩዋንዳዊያን በተለይ በሰብዓዊ መብት ማስከበር ላይ ለሚያሳዩት ትኩረት መሠረት ጥሎ ማለፉን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከስድስት እስከ አስር ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች የተገደሉበት የግጭቶች አዙሪት ውስጥ ገብታ ነበር፡፡

ግጭቶችን ለመፍታት በተፋላሚ ወገኖች መሪዎች መካከል የሰላም ስምምነቶች የተደረገ ሲሆን የተጎዱትን ሕዝቦች ለመካስ እና ዘላቂ እርቅን ለመፍጠር ይህንኑ የሽግግር ወቅት ፍትሕ ተግብረዋል፡፡

የላይቤሪያ የአስራ አምስት ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት እንዲሁም ሴራሊዮን እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1991 እስከ 2002 ካጋጠማት አስከፊ የሆነ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ዜጎች መጠነ ሰፊ እንግልት የደረሰባቸው ሲሆን በሽግግር ፍትሕ ሂደት መተማመንና እርቅ ፈጥረው ሀገረ መንግስት ገንብተው ቀጥለዋል፡፡

በተጨማሪም በዩጎዝላቪያ፣ ቺሊ፣ ጋምቢያ እና ሌሎች ሀጋራት ላይ ተበዳዮች የተካሱበት አጥፊዎች በሒደቱ ፍርድ ያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እንደ ማሳያ ከላይ የተጠቀሱትን ሀገራት አነሳን እንጂ በርካታ የዓለም ሀገራት ዘላቂ ሰላም፣ ፍትሕና ዕርቅን ለመፍጠር ሒደቱን ተጠቅመውበታል፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የጀመረችው የሽግግር ፍትሕ ሒደት በአግባቡ ሲተገበር ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የተሻለ ነገን መፍጠር የሚችል ሲሆን ትኩረቱን ልማት ላይ የሚያደርግ እና ቅራኔ የሌለው ማኅበረሰብ ለመፍጠር ያስችላል፡፡ ሒደቱን ከተገበሩ ሌሎች ሀገራት የተስተዋለውም ውጤት ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡

በሽግግር ፍትሕ ሒደት ወቅት ለታሰበው ተልዕኮ ውጤታማነት የምሁራን፣ የሚዲያ እንዲሁም የኅብረተሰቡ ሚና ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመተግበር ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል፡፡